በዩኒቨርሲቲው የሦስት ዓመታት የሠላም፣ የልማትና የለውጥ ጉዞ ስኬቶችና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ከወላይታ ዞን ከተለያዩ መዋቅሮች ከተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው በሦስት ዓመታት ውስጥ በተከናወኑ የሰላምና የልማት ጉዞ ስኬቶች እንዲሁም ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በተካሄደ የምክክር መድርክ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ ባለፉት 3 ዓመታ ዩኒቨርሲቲውን ተወዳዳሪ፣ አረንጓዴ፣ ጽዱ፣ ሠላማዊ እና ሕብረ-ብሔራዊ ለማድረግ በተቀናጀ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውን መንግስት ድህነትንና ኋላቀርነትን በማስወገድ በሃገሪቱ የት/ት ተደራሽነትን፤ ፍታዊነትን፤ ተገቢነትንና ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ ባደረገው ሁሉ አቀፍ ርብርብ በ1999 ዓ.ም በአዋጅ ከተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ አውስተዋል፡፡
በ1999 ዓ.ም 801 ተማሪዎችን ብቻ ተቀብሎ በ16 ፕሮግራሞች ሥራ የጀመረው ዩኒቨርሲቲው በአሁን ሰዓት በሶስት ካምፓሶች በሰባት ኮሌጆችና ሶስት ት/ቤቶች በ58 የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በ55 የ2ኛ ዲግሪ፤ በ2 ስፔሻሊቲ እና በ6 የ3ኛ ዲግሪ (በዶክተሬት ዲግሪ) በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች ከ38 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል ሲሉም ፕ/ር ታከለ ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ በመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ዕምቅ የመልማት አቅም፤ ሀብት፤ ሥነ-ምህዳር፤ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ተደራሽነት መሰረት በማድረግ በተሰጠው ተልዕኮ እና ልየታ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መመደቡን ገልጸዋል፡፡ 
በግብርና ፤ በጤና፤ በኢንጂነሪግና ቴክኖሎጂ፤ በከርስ ምድር ጥናትና ሥነ-ሰብ የትምህርት መስኮች የአካባቢውን ዕምቅ የመልማት አቅም መሰረት በማድረግ በሂደት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን አቅጣጫ እንዲሆን መወሰኑንም ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮችንና ባለፉት አመታት ያልተሻገራቸውን ችግሮችን በስፋትና በጥልቀት በመተንተን ቁልፍ አጀንዳዎችን በመለየት የ10 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ (2013-2022ዓ.ም) አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው በ2022 ዓ.ም ቴክኖሎጂ መር የግብርና እና የጤና ልህቀት ማዕከል ለመሆን ራዕዩን ሰንቆ እየሰራ መሆኑንም ፕ/ር ታከለ አሳውቀዋል፡፡
መልካም አስተዳደር የሰፈነበትና የሰላም ተምሳሌት መሆን፤ከአገልግሎት ሽፋን ወደ አገልግሎት ጥራትና ልህቀት መሻገር፤ከንድፈ-ሀሳብ ተኮር ወደ ተግባር ተኮር ት/ትና ምርምር መሻገር፤ ከማኅበረሰብ አገልግሎት ወደ ችግር-ፈች ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት መሻገር፤የተቋሙን አለማቀፋዊነትና አጋርነት ማሳደግ፤ ከተለምዷዊ አሰራር ሥነ-ዘዴዎች ወደ ዲጂታል አሰራር ሥነ-ዘዴዎች መሻገር (E-University) ዩኒቨረርሲቲው ቁልፍ የትኩረት አጀንዳዎች መሆናቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የመድረኩን ዓለማ ሲናገሩም በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሦስት ዓመታ በተከናወኑ ዋና ዋና የሰላምና የልማት ጉዞ ስኬቶች እና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ከወላይታ ዞን ከተለያዩ መዋቅሮች ለተወጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር የሃሳብ ግልፅነትና የጋራ ስምምነት ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ እንደገለጹት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 3 ዓመታት በመማር ማስተማር፣ በችግር ፈቺ ምርምር፣በማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ያለ ስኬታማ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ቁልፍ የትኩረት መስኮችን በመለየት በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ ስራ ሊሰራ የቻለውም የህብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት ለይቶ ከማህበረሰቡ ጋር ለመስራት የሚያችል ተግባት በፍጠር የመጣ ለውጥ ነውም ብለዋል ዶ/ር እንድሪያስ  ፡፡
እንደ ተቋም የተጀመሩ መልካም ተግባር ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ያሉት ምክትል ቦርድ ሰብሳቢው፤ በተቋሙናተቋሙ በሚገኝበት አካባቢ ሕብረ-ብሔራዊነት እንዲጎለብት ሁሌም በትጋት መስራት አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የዕውቀት ማዕከል የሆነው ተቋማችን እድገቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም ለሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲሁም ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሌም እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ዶ/ር እንድሪያስ ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በሃገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተጀመሩ በትብብር የመስራት ማዕቀፍን በማሳደግ የተቋሙን ዓለማቀፋዊነት የላቀ እምርታ ላይ ለማድረስ ሁላችንም በትብብር የመስራት ባሕላችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል በማለትም ዶ/ር እንድሪያ ጌታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወኑ አበይት የሠላም፣ የልማትና የለውጥ ጉዞ ስኬቶችና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ቀርቦ ከወላይታ ዞን ከተለያዩ መዋቅሮች ከተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ሳይንስና ከፍተኛ ት/ት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና በቻይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የተከበሩ አምባሳር ተሾመ ቶጋ ተገኝተዋል፡፡ 
መድረኩ በወላይታ ባህላዊ እና ዘመናዊ ኪነት ባንድ በቀረቡ ጣዕመ ዜማዎች የደመቀ ሲሆን፤ የወላይታ ዞን የሀገር ሽግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ለሀገራችን ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የምረቃ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ በዩኒርሲቲው የተከናወኑ አበይት ተግባራት በተሳታፊዎች እንደሚጎበኙ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አሳውቋል፡፡

Category: 

WSU MAP

Visitors

  • Total Visitors: 337390

CONNECT WITH US

We are on Social Networks. Follow us & get in touch.

The offitial address of the university:-

Twitter     @WSodoUniversity

Facebook